የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 2ኛውን የአማራ ክልል የግብርና ፎረም አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪልና የውሀ ምህንድስና ፋኩሊቲ 2ኛውን የአማራ ክልል የግብርና ፎረም “Small Scall Irrigation and Agricultural Technologies for Sustainable Development in Amhara Region” በሚል ርዕሰ ጥር 8/2010 ዓ/ም በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በዚህ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማትና አቅም ግንባታ ድጋፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ማማሩ ጽድቁ ናቸው። እንደርሳቸው ገለጻ ይህ ፎረም የተቋቋመው በአማራ ክልል አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ላይ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን ለማስወገድ፣ በግብርናው መስክ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ እንከኖችን ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ በክልሉ ላይ ምርትን ለመጨመር እንዲሁም ሞዴል የሰርቶ ማሳያ ቦታዎችን በማቋቋም የግብርና ሰርቶ ማሳያዎችን በመስራት ለማሳየትና በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው መንግስታዊ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት በጋራ ተናበው እንዲሰሩ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። በአማራ ክልል በመስኖ ልማት ላይ በተለይም መስኖና ኢነርጂ፣ ግብርና ቢሮ፣ አውስኮድ፣ አመልድ፣ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነና በተለይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከኖርዌይ መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲያካሂድ እንደቆየና ፎረሙም ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነና 2ኛውን የአማራ ክልል የግብርና ፎረም እንዳዘጋጀ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለና በተለይም ለግብርና ስራ አመች እንደሆነ የገለጹት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዜና ማርቆስ ባንቴ ናቸው። አክለውም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በክልሉ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየሰራ እንደሆነና በመስኖ ልማት እንዲሁም አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሆነና በተለይም በክልሉ ላይ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ምርምር በማካሄድ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው በዚህ ጉባኤ ላይም በክልሉ ውስጥ አነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ስራዎች እንዴት መሰራት እንዳለበትና በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በአነስተኛና ጥቃቅን መስኖ ልማት ስራዎች ላይ የራሱን ድጋፍ እንደሚያደርግና በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ግብርና የግብርና ባለሙያዎችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን የተለያዩ የሙያ መስኮችን የሚመለከትና የሚዳስስ ጉዳ እንደሆነ የተናገሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሲቪልና የውሀ ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፎረሙ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ናቸው። አክለውም በዚህ ፎረም ላይ ለአርሶ አደሮች የሚጠቅሙ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ብሎ በመለየትና የክልሉን ህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለመስራትና ምን እየተካሄደ ነው? ምን አይነት ጥረቶች አሉ? ማን ማን ጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው? ምን አይነት ሀሳቦች አሉ? የሚለውን ለመገንዘብ እና ፖሊሲ አውጭዎችና አስተግባሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አጋር አካላት ከዚህ ውይይት ላይ ግንዛቤ በመውሰድ እንዲሰሩና የጋራ ግንኙነታቸውን እንዲያሰፉ ለማድረግ እንደሚያግዝም አስተባባሪው ተናግረዋል።