የሰላምና ልማት ማዕከል ዘላቂ የውይይት

የሰላምና ልማት ማዕከል ዘላቂ የውይይት ፕሮጀክት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በሰላም ዙሪያ ተወያየ፡፡
==============================================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘላቂ የውይይት ፕሮጀክት ቁጥራቸው ከስድስት መቶ በላይ ከሚሆኑ የማህበሩ አባል የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር በጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ኤደን አምሳሉ ለተማሪዎች መልክት ያስተላለፉ ሲሆን የአዳራሹን በተማሪዎች መሙላት ሲያዩ መደሰታቸውንና ይህ ሁሉ የሰላም ሰራዊት እያለ በተቋማችን በሰላም ዙሪያ ምንም አይነት ስጋት አይኖርም ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ የሰላም መድረክ የታላቁ ሙሁር የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ ከአሜሪካ እና በተባበሩት መንግስታት የወጣት አደረጃጀት ኃላፊ የአቶ ባንታዩ ደምሴ ስለ ሰላም ያስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ለተማሪዎች ቀርቧል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ በላይነህ ማዘንጊያ እና የፕሮጀክቱ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ይበልጣል አሰፋ በመድረኩ ተገኝተው ስለሰላም አስፈላጊትና በቀጣይነቱ ዙሪያ ለተማሪዎች ተናግረው በምክክር መድረኩ ላይ የተገኘው የተማሪዎች ቁጥር ያልጠበቁትና ማዕከሉ አንግቦት ለተነሳው አላማ መሳካት ትልቅ አስተዋፃ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ብዝሀነት የሚያስተናግድ በመሆኑ በቀጣይነት ዘላቂ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀትና በሰላም ዙሪያ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰሩ የውጭ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ተማሪዎችም በግሩፕ በመሆን በመማር ማስተማር ውስጥ ሰላም እና መከባበር አስፈላጊ በመሆኑና በቀጣይነቱም ዙሪያ ውይይት አድረገው ሀሳቦቻቸውን ለማዕከሉ አቅርበዋል፡፡ ይህ የሰላምና ልማት ማዕከል በአፍሪካ እና በአሜሪካ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሰላምና በአብሮነት እሴቶች ዙሪያ የሚሰራ ድርጅት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ የሰላም መድረክ ከUSAID የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ከLife and peace institute ጋር በመተባበር በየሁለት ሳምንቱ የሚካሄድ ሲሆን የሰላም እና የአብሮነትን እሴት ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡