2012 ዓ.ም ገና በባሕር ዳር እንደ ቤቴ

ባሕር ዳር እንደ ቤቴ የገና በዓልን ከተማሪዎች ጋር አከበረ
**********************************************
ከተመሰረተ አንድ አመትን ባስቆጠረው ባሕር ዳር እንደ ቤቴ በተሰኘው ፕሮጀክት ስም በባህር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ መኖሪያ ቤት ከ30 በላይ የሚሆኑ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በታደሙበት የገና በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከበረ፡፡
 
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የባህር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ሲሆኑ የዕለቱን ዝግጅት ጨምሮ ለከተማው ህብረተሰብ ሰላም እና መረጋጋት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሀገር ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን አመስግነዋል፡፡ አቶ አማረ አክለውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በከተማዋ ቆይታቸው ሰላማዊ እንዲሆን የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማወያየት የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ አውሰተው ከፍተኛ አመራሩም የተማሪዎች ችግር ችግሩ የሆነ ስለ ሰላማቸውና የተረጋጋ የትምህርት ድባብ እንዲፈጠር ተግቶ እየሰራ የሚገኝ መኖኑን ገልፀዋል፡፡ የዕለቱን ሁነት ሲገልፁም የባሕር ዳር እንደ ቤቴ ፕሮግራም ፈቃደኛ ተማሪዎችን ወደ ቤት በመውሰድ እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸውና እንደ ወላጅ የሚመክር ቤተሰብ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከሚደረግው ተግባር ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኜ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አሁን ባለው ወቅታዊ ጉዳይ አነሰም በዛ በተማሪዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳይደርስብ ቆይተናል ሲሉ ፈታኙን ጊዜ ገልፀዋል፡፡ እለቱን አስመልክቶም ባሕር ዳር እንደ ቤቴ ፕሮግራም በፈቃደኛ ወላጆችና ወጣቶች ትስሰር 1ኛ ዓመት እንደሞላው ጠቅሰው በእለቱ እንደተደረገው በአንድ ግለሰብ ከ30 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደቤታቸው ቆጥረው በዓሉን እንዲያሳልፉ ማድረግ መቻሉ አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዓሉን ስናከብር ተማሪዎች ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እንደመምጣታቸው ቤተሰብን የሚናፍቅ ተማሪ እና ቤተሰብ ለመመስረት የሚፈልግ ወላጅን ለማገናኘት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በጎ አጋጣሚ ሲሉ የባህር ዳር እንደ ቤቴ ፕሮግራምን ገልፀውታል፡፡
የባህር ዳር ከተማ የደራሲያ ማህበር ሊቀመንበር ሊቀ ሂሩያን በላይ መኮነን የሀገር ሽማግሌዎችን ወክለው እንደተናገሩት በርካታ ተማሪዎችን በማሰባሰብ በአንድ ላይ በዓል እንድናከብር ያደረጉትን አቶ አማረ አለሙ አመስግነው ባህር ዳርን ከሚያውቁበት ከ1950ዎቹ ጀምሮ በትምህርትም ሆነ በስራ ሰዎች ሲሰባሰቡ በፍቅር ያስተናገደች ከተማ መሆኗን መስክረው ባሕር ዳር እንደ ቤቴ ሳይሆን ከተማዋን ቤቴ እንዲሏት አባታዊ ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡
 
የዘንድሮውን የባህር ዳር እንደ ቤቴ ፕሮግራም የተለየ በሚያደርግ ሁኔታ በኢትዮጵያ ህክምና ተማሪዎች ማህበር በባህር ዳር ቅርንጫፍ የበጉ አድራጎት የስራ ዘርፍ ከበሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፈለገ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ታካሚዎችንና አስታማሚዎችን በማሰባሰብ በዓልን እንደቤታቸው እንዲሰማቸው በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል፡፡
 
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እንደቤታቸው እንዲሰማቸው የተሸለ እየሰሩ ያሉ አመራሮች በከተማው ወጣቶች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡