የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD) የመስክ ምልከታ አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD) የክልሉ አርሶ አደሮች ጥራት ያለው ዘር
እንዲያገኙ እና የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ከአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲት፣ ከአዴት ግብርና ምርምር፣
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እንዲሁም በዘርፉ ተሰማርተው ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡
በመስክ ምልከታው ወቅት ከባሕር ዳር ፣ከጎንደር ፤ከደብረ ታቦር ፤ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም
ከምዕራብ ጎጃም፤ ከአዊ፤ከምስራቅ ጎጃም፤ከሰሜን ጎንደር፤ከደቡብ ጎንደር ፤ከሰሜን ወሎ ዞኖች የሚመለከታቸው
ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በክልሉ ውስጥ በዘር ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የሥራ ክፍሎች በመስክ ምልከታው
ወቅት ተገኝተዋል፡፡
በሰሜን አቸፈር ወረዳ ሳንክራ ቀበሌ ላይ በተደረገው የመስክ ምልከታ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ እና
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD/ አስተባባሪ የሆኑት
ዶ/ር ደረጀ አያሌው የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD) በዋነኛነት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከማገዝ
አኳያና የዘር ስርዓትን ለማሻሻል ከዛሬ 7 ዓመት በፊት የተቋቋመ እንደሆነ እና በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመት ውስጥ
የተሻሉና ጥራት አላቸው ተብለው የተመረጡ ዘሮችን በማባዛት በክልሉ ውሥጥ እንዲሁም ከክልሉ ውጭ ምርትና
ምርታማነትን ከፍ ማድረግ ላይ እየሰራ እንደነበር እና እያደገ የመጣውን ማህበረሰብ ለመመገብ ከፍተኛ የሆኑ ስራዎች
ሲሰራ እንደቆየ ጠቁመው አሁንም የውል ጊዜውን ለሶስተኛ ጊዜ በማራዘም ከዚህ በፊት ያልተነኩ ስራዎችን
ለመስራትና ከዚህ በፊት ትኩረት ሳይሰጠው የቆየውን የኢ-መደበኛወን የዘር ሥርዓት ለመደገፍ እየሰራ እንደሆነና በተለይ
በዚህኛው ዙር ሴት አርሶ አደሮችን በተለየ ሁኔታ ለመደገፍ እያመቻቸ የቆየ ቢሆንም በዚህ ዓመት ግን ወደተግባር
እንደተገባ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በኔዘርላንድ መንግስት የሚደገፍ ሆኖ
በኢትዮጵያ ላይ በሚገኙ አራት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማለትም ባሕር ዳር፣ ሀሮምያ፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ
ዩኒቨርስቲ እንዲሁም የኦሮሚያ የዘር ልማት ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ላይ የሚታየውን የዘር ብዜት ችግር
ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ እና ማዕከላቱ ለማሕበራት፣ ለግል ዘር አባዦች እንዲሁም ለዘርፍ ባለሙያዎች
የስልጠና፣ የልምድ ልውውጥ፣ የገንዘብ እርዳታ፣ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት፣ ማስተዋወቅና የምርምር አገልግሎት
በዋነኛነት ሲሰጡ እንደቆየና አሁንም እየሰጠ እንደሚገኝ አስተባባሪው ገለፀዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD) ከስድስት ወረዳዎች 1200 አርሶ አደሮች
በመምረጥ የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን 1195 ወደ ስራው ሲገቡ 5 ያህሉ
በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ ሳይገቡ እንደቀሩ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በዳጉሳ፣
በስንዴ፣በጤፍ፣በቆሎ፣በአተር፣በገብስ፣ማሽላ ወዘተ የሰብል ዝርያዎች ላይ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው በተለይ የዳጉሳን
ምርት ላማሳደግ 19 የዳጉሳ ዝርያወችን በማቅረብ ለእያንዳንዱ አርሶ አደር 3 የዳጉሳ ዝርያዎችን በመዝራት የትኛው
የተሸለ እና ምርታማ እንደሆነ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ መለየት እና በሚቀጥለው ዓመት የበለጠ በማጠንከር ለመስራት
እየተዘጋጁ እንደሆነ የገለፁት የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (ISSD) ህብረት ስራ ባለሙያ የሆነው አቶ ሚኒሊክ
ከፋለ ናቸው፡፡ ባለሙያው አክለውም አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በኤክስቴሽኑ መርኀ ግበር ላይ ያልተካተቱ ነገር ግን
የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሰብሎች ላይ ትኩረት አደርገው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

2

በሰሜን አቸፈር ወረዳ በሰብልም ሆነ በምርት ሽፋን ከበቆሎ ቀጥሎ በሁተኛ ደረጃ የሚገኘውን የዳጉሳ ዝርያ ማህበረሰቡ
እንደ ጤፍ፣ስንዴ ወዘተ በመደበኛው የዘር ስርዓት ዘር የማይቀርብለት በመሆኑ እስከ አሁን ድርስ ተጠቃሚ ሳይሆን
እንደቆየ እና ነገር ግን ይህን ችግር በመረዳት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮግራም /ISSD/
ለመስራት እያደረገ ያለው ጥረት ሊደነቅ እንደሚገባ የተናገሩት የሰሜን አቸፈር ወረዳ የሰብል ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘመነ
ወርቁ ናቸው ፡፡
በመስክ ምልከታው ከሰሜን አቸፈር ወረዳ የግል ዘር አብዥ ድርጅት (እናጌት) እንዲሁም ከቡሬ ወረዳ በቀጥታ የዘር
ግብይት ስርዓት የተሳታፊ የዘር ብዜት ህብረት ሥራ ማህበር (ሰርተን እንደግ) የመስክ ምልከታው የተካሄደባቸው
ማህበራት ናቸው፡፡ በመስክ መልከታው ወቅት አግኝቼ ቃለ መጠይቅ ያደረጉላቸው አርሶ አደር በትሀ አስማረ እና
ይህዓለም ተሰራ እንዳሉት በመጀመሪያ ሲነገረን ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ተቸግረው እንደነበር እና መንግስት ያመጣው
ይጠቅም እንደሆነ እንጂ አይጎዳም በማለት ለሁለት ቀን የተሰጠውን ስልጠና እንደወሰዱ እና ወደስራ እንደገቡ ጠቅሰው
ከቡቃየው ጊዜ ጀምሮ እስከ ፋሬው ድረስ ያለው ሄደት በጣም አስደሳች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ከመስክ ምልከታው የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በማንሳት የተለያዩ ውይይቶችና የመፍትሄ
አቅጣጫዎችን ተሳታፊዎቸ አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጂ
ዲን የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አዲሱ የመስክ ምልከታው አይን ከፋች እንዲሁም አስተማሪና አበርታች እንደነበር ገለፀው፤
ዩኒቨርሰቲው ከመማር ማስተማሩ ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝ እና ለአርሶ
አደሮች እንዲሁም በዘር ዘርፍ ለሚሰሩ አካላት የረጅም እንዲሁም የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ እና ከጐናቸው
በመቆም በጋራ እንደሚሰራ አሳስበዋል፡፡